1, መግቢያ ባጭሩ
የአንድ ሀገር የመጨረሻ ዳኝነት ሰጪ አካል የራሱን አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ የመሻር ሥልጣኑ እጅግ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ቢሆንም የዳኝነት ነፃነትና የሕግ ዝግመተ ለውጥ ወሳኝ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ ሥልጣን በሁለት የሕግ የበላይነት መሠረታዊ መርሆዎች መካከል ያለውን ሚዛን ለመጠበቅ የሚያገልግል ወሳኝ የዳኝነት መሳሪያት ነው፡፡ እነርሱም በአንድ በኩል የሕግ መረጋጋትና ተገማችነት (Legal stability and predictability/Certainty) እና በሌላ በኩል ደግሞ ሕግ ተለዋዋጭ ፍትሕን የማረጋገጥ (Flexibility for Justice) ግዴታ ናቸው። በመሆኑም አንድን አስገዳጅ ትርጓሜ የመሻር ውሳኔ ቀላል የአቋም ለውጥ ሳይሆን የቀደመውን የፍርድ ውሳኔ ሕጋዊ ተፈጻሚነት የሚቀር ሃይል ያለው በመሆኑ ጥልቅ የዳኝነት ተግባር ነው። ይህ ጥልቅ የዳኝነት ተግባር በዋናነት በሚከተሉት መሠረታዊ ምክንያቶች ይደገፋል፡፡ የመጀመሪያው ስህተትን ማረም ሲሆን፣ በዚህም ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል የሰጠው ውሳኔ/ትርጓሜ በተሳሳተ አመክንዮ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ሲገነዘብ ታሪካዊ ስህተቱን ያስተካክላል፡፡ ሁለተኛው ህግን ከዘመኑ ጋር ማጣጣም ነው፡፡ ይህም ህጉ ከአገራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች ጋር አብሮ የሚራመድ ህያው ሰነድ እንዲሆ ያስችለዋል ተብሎ በብዙሃኑ የዘርፉ ምሁራን ይታመናል፡፡ ሶስተኛው ደግሞ የአስተምህሮ ውህደት ሲሆን በዚህም ፍርድ ቤቱ በራሱ ውሳኔዎች መካከል የተፈጠረን ተቃርኖ በማስወገድ የህግ ወጥነትን ለማረጋገጥ ያስችለዋል የሚለው ስለመሆኑ የምርምር ስራዎች ያሳያሉ፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰባት ዳኞች ተሰይሞ በሰበር መዝገብ ቁጥር 242314 ላይ የሰጠው ውሳኔ፣ በተለይ የዚህን ሦስተኛ ምክንያት ማለትም የአስተምህሮ ውህደትን የማስፈን ዓላማ ቀጥተኛ ማሳያ ነው። ውሳኔው በራሱ በሰበር ውሳኔዎች መካከል የነበረን ቅራኔ በማስወገድ የአስተምህሮ ወጥነትን የማረጋገጥ ግቡን ያሳካ ቢሆንም ይህ ሂሳዊ ትንታኔ እንደሚሞግተው ይህንን ያደረገው ጥብቅ የሆነ የሕግ ወግ አጥባቂነት (Legal Formalism) አስተሳሰብን በአፅንዖት በመከተል ነው። ይህ አካሄድ በማህበረ-ህጋዊ (Socio-Legal) መነጽር ሲታይ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት በወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ሰነዳዊ ይዘት ላይ ብቻ በማተኮር ከሀገሪቱ ተጨባጭ ማኅበራዊ እውነታ የተፋታና ፍትሐዊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ውጤት አስከትሏል። በመሆኑም ይህ ጽሑፍ ውሳኔው የአስተዳጅ ሕግ ትርጉሞችን ወጥነት ያረጋገጥ ነው በሚል ምክንያት ውዳሴ ባይነፍገውም የማኅበረሰባዊ ፍትሕን ሚና ችላ ማለቱን በተከታዮቹ ክፍሎች ለማሳየት ይሞክራል።
የአስተምህሮው አውድ፡ በፍ/ህ/ቁጥር 1179 ድንጋጌ ትርጓሜ ላይ የነበረውን ተቃርኖ መፍታት
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰባት ዳኞች ተሰይሞ በሰበር መዝገብ ቁጥር 242314 ላይ የሰጠው ውሳኔ፣ በኢትዮጵያ የንብረት ህግ አስተምህሮ ታሪክ ውስጥ አንድ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡ ችሎቱ ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የዳኝነት ትርጉም አስተምህሮ አለመጣጣም /Contradition/ ለመፍታት ጥረት ማድረጉን ውሳኔው የሚያስገነዝብን ጉዳይ ቢሆንም ለህግ ወግ አጥባቂነት ፍልስፍና (formalism) ወሳኝ ቦታ መስጠቱን ሊያስቀረው አልቻለም፡፡ በዚህም በህንጻ ላይ ያለን መብት ህንጻው ካረፈበት መሬት ጋር ካለው ማንኛውም ህግ-አልባ ጥያቄ ጋር ያለውን ግንኙነት ግልፅ አድርጎ ህጋዊ ሰነድ የያዘውን ወገን ህጉ ጠባቂ ስለመሆኑ በግልፅ ለይቶ አንድ ወጥ የሆነ አቋም አሳውቋል፡፡ ምንም እንኳን ውሳኔው እጅግ አስፈላጊና ተፈላጊ የሆነን የህግ ግልጽነትና የዳኝነት ወጥነት የሚያመጣ መሆኑ እሙን ቢሆንም ማህበረ-ህጋዊ አንድምታዎቹ ግን እጅግ አሳሳቢ ናቸው፡፡ ውሳኔው ለዘመናት የቆዩ የማህበረሰብ ልማዶችን፣ የቤተሰብ ስምምነቶችንና የፍትሐዊነት መርሆዎችን ወደ ጎን በመተው በሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ለሚሰጡ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዶች የበላይነት በመስጠቱ በወረቀት ላይ ባለው ህግና በሚሊዮኖች ህይወት እውነታ መካከል ጥልቅ የሆነ ልዩነትን የፈጠረ ስለመሆኑ በሰፊው የሚታወቀው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በራሱ አስረጅ ነው፡፡ አዲሱ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ይህንኑ ማህበረሰባዊ ሀቅ ያለማገናዘቡ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስን የሚጋብዝ እና አዲስና አደገኛ የሆነ የመሬት ይዞታ ዋስትና ዕጦትን የሚፈጥር መሆኑ ይገመታል፡፡
ከላይ እንደተጠቆመው በዚህ ውሳኔ የችሎቱ ዋነኛ ስኬት ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው እርስ በርሳቸው የሚጋጩ አስገዳጅ የህግ ትርጉሞች ቁጥር በበረከተበት የአስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓት ውስጥ ይኸው ስርዓት ሲቋቋም እንደ ግብ ከታሰቡት ዓላማዎች መካከል በዋንኝነት የሚጠቀሱትን ተመሳሳይ (consistency) እና ወጥ የሆነ (uniform) የዳኝነት ስርዓት ማስፍን የሚሉትን ለማሳካት ጥረት ማድረጉ ነው፡፡ የአስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓት ከተቀረፀበት ከሰኔ 07 ቀን 1997 ዓ/ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ፤ ለዓመታት፤ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በፍትሐ ብሔር ህግ አንቀጽ 1179 ድንጋጌ ትክክለኛ አተገባበር ላይ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ውሳኔዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ሰበር ሰሚ ችሎቱ ራሱ ቁጥሩ ከላይ በተጠቀሰው መዝገብ ፍርድ ላይ ያሰፈራቸው መዛግብት በቂ አስረጅ ናቸው፡፡ ይህም በችሎቱ የህግ ትርጉም ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የህግ እርግጠኝነትና ተገማችነት ዕጦትን ፈጥሮ የነበረ መሆኑ የሚታመን ነው፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎቱ ባለሰባት ዳኞች ችሎት ይህንን ችግር በመገንዘብ ግልጽ፣ የማያሻማ እና በህገ-መንግስታዊ መሰረት ላይ የቆመ ነው ያለውን የዳኝነት አስተምህሮን ለማስቀመጥ ጥረት ማድረጉንም የውሳኔው ሙሉ ይዘት በራሱ አስረጅ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ይመስለኛል፡፡ በውጤቱም በመሬቱ ይዞታ ህጋዊ ባለመብት ሙሉ እውቅናና ያለህጋዊ የሰነድ ስምምነት በይዞታው ላይ ህንጻ የገነባውን ወገን መብት ሲጠብቅ የነበረውንና የህንጻ ባለቤትነትን ከመሬቱ ላይ ተለይቶ ከማይነቀል መብት ጋር ሲያቆራኝ የነበረውን የቀደመ አስገዳጅ የህግ ትርጓሜ ለውጧል፡፡ ችሎቱ በውሳኔው እንዳመለከተው ይህ የቆየ አረዳድ ከ1967 ዓ.ም. የመሬት አዋጅ እና በ1987 ዓ/ም በፀደቀው፤ የመሬት ባለቤትነት መብት የመንግስት እና የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው ከሚለው ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ በኋላ በ1952 ዓ/ም በወጣው የፍትሐ ብሔር ህጉ የተካተቱት የመሬት ይዞታ ጥበቃ የሚያደርጉና የሚያስለቅቁ ድንጋጌዎች የተፈፃሚነት ዋጋ አጥተዋል ከሚል የተሳሳተ መነሻ ላይ የተመሰረተ ነበር ተብሎ ሊወስድ የሚችል ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ በግልጽ ህግጋት የማይቀሩና የማይለወጡ ሊነኩ አይገባም የሚለውን ፍልስፍና የሚያራምደውን የህግ ወግ አጥባቂነት/ Legal Formalism/ የላቀ የአተረጓጎም ስልት አድርጎ በመውሰድ በፍቃድም ቢሆን በሌላ ሰው ይዞታ ላይ ህንጻ መገንባት፣ በመሬቱ ይዞታ ላይ ለገንቢው ምንም አይነት የባለይዞታነት መብት እንደማያስገኝ አረጋግጧል፡፡ የገንቢው መብት ህንጻው ሲፈርስ በሚከፈለው ካሳ ላይ ብቻ የተወሰነ መሆኑን ችሎቱ ይፋ አቋሙ መሆኑን ወስኗል፡፡
ችሎቱ አዲሱን የህግ ትርጉም ምክንያት ጠንካራ ለማድረግ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በ6ኛ የፓርላማ ዘመን 2ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በመ/ቁ. 106/15 በሰጠው ውሳኔ የህገ-መንግስት ትርጓሜ ጋር ያቆራኘው ሲሆን ለጉዳዩ አግባብነት አለው በሚል የለየውን ፓራግራፍም በፍርድ ሀተታው ውስጥ አስቀምጧል፡፡ ችሎቱ ይህንን የህገ-መንግስት ትርጓሜ ከጉዳዩ ጋር ይመሳሰላል በሚለው የራሱ አረዳድ በመስለው ከአተተው በኋላ እንደ አስገዳጅ ህገ መንግስታዊ ትርጉም እና መሰረት በመጠቀም፣ የመሬት የመጠቀም መብት የሚመነጨው ከመንግስት ብቻ ስለመሆኑ አረጋግጧል፡፡ የግል ድርጊቶች ለምሳሌ ለመገንባት ፍቃድ መስጠት በህግ እውቅና ያለው የመሬት መብትን ከህግ አግባብ ውጪ ሊፈጥሩ እንደማይችሉ በማረጋገጥ ውሳኔውን ከቀላል የህግ ትርጓሜነት ወደ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ደረጃነት እና ግዴታነት ከፍ አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም ገንቢን ሲደግፉ የነበሩትን የቆዩ የሰበር ችሎቱ አስገዳጅ ውሳኔዎች በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ መብት ለማግኘት የሚያስችል አዲስ መንገድ መፍጠራቸውን ተገንዝቧል፡፡ ይህም በፍትሐ ብሔር ህጉ የተቀመጡትን ጥብቅ የህግ ሥርዓቶች በቀጥታ የሚጥስ እንደነበር ገልጿል፡፡
ችሎቱ "ፍቃድ" የሚለውን ቃል ትርጉም ከአዲሱ ዐውደ ጥበባዊ የሕግ መዝገበ ቃላት ከወሰደ በኋላ በድርጊት የሚገለፅ ዝምታ ወይም ያለመቃወም የመሬት መብትን ለማስተላለፍ መሰረት ሊሆን አይችልም፣ የንብረት ምዝገባና ዝውውር ስርዓቱን መጠበቅ አለበት የሚል አንድምታ ያለውን ድምዳሜም ይዟል፡፡ ይሁን እንጂ የቃላት አተረጓጎም ምርጫ የታከለበት ከመሆኑ በተጨማሪ ችሎቱ በመሬት ላይ መብት የፈጠሩት ውሳኔዎች በተቃራኒው ፈቃድን ማለትም ማድረግን ወይም መፈጸምን መሰረት እንዳደረጉ፣ ለቀደመው ውሳኔ መሰረት በተደረጉት የሕጉ ድንጋጌዎች የማይታወቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ መብት ሊፈጠርበት የሚችለውን አግባብ የመለወጥ ውጤት ያለው ትርጓሜ ስለመሆኑ አትቶ ሕጋዊ ገደብ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ባለመሬት ወይም ባለይዞታ በመሬት ላይ መብት ለመፍጠር ከፈቀደ በፍ/ሕ/ቁ. 1723 ስለውል አጻጻፍ የተደነገገውን መከተል አስፈላጊ ነው ሲል በምክንያትነት ሲያስፍር ግን አንድ ባለይዞታ ግንባታ ከአስፈረበት ይዞታ ላይ ያለውን ባዶ ቦታ ቆርሶ በፍ/ህ/ቁጥር 1723 አግባብ ለማስተላለፍ ወደ ሚመለከተው ውል አዋዋይ አካል ቢሄድ ከህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ጭምር ቅቡልነት ሊያገኝ የማይችልበት አግባብ መኖሩን፣ እንዲሁም የመንደር ውልን መሰረት ያደረገ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል በተዋዋይ ወገኖች መታመንን በሚመለከት ሰበር ችሎቱ ከሰጣቸው በርካታ አስገዳጅ ትርጉሞች አንፃር ጉዳዩ የሚታየበት እና በተለየ መልኩ ሊፈፀም የሚችል መሆኑን ሳያመላከት ማለፉ ወደፊት ውስብስብ የህግ ክርክሮች ሊያስነሳ ይችላል፡፡
3. ማህበረ-ህጋዊ ትንታኔ፡ የሕግ ወግ አጥባቂነት ፍልስፍና /Legal Formalism/ እና የማህበራዊ እውነታ /Sociological Jurisprudence/ ግጭት
ምንም እንኳን ውሳኔው በበርካታ ህግጋት እና ድንጋጌዎቹ የታጀበ ቢሆንም ቁልጭ ያለና ሁሉንም የሚያስማማ የአስተምህሮ ጥራት አለው ብሎ ለመውሰድ ግን የሚያስቸግር ሁኖ ይታያል፡፡ እንዲሁም ጥብቅ የሆነውን የህግ ወግ አጥባቂ ፍልስፍና (ፎርማሊዝም) መነጽር በብቸኝነት የትርጉሙ ስልት አድርጎ በመውስድ ጥልቅ ፋይዳ ያላቸውን ማህበራዊናባህላዊ ስምምነቶች በቸልታ ማለፉ ዋነኛ ድክመቱ ሁኖ ይታያል፡፡ የውሳኔው ትልቁ ስህተት እነዚህ ክርክሮች በአብዛኛው የሚነሱበትን አውድ ከግምት ውስጥ አለማስገባቱ ነው፡፡ ይህ አዲሱ የህግ ትርጉም የተሰጠበት መዝገብ ራሱ በወራሾች መካከል የተነሳ የውርስ ክርክር መሆኑ፣ የችግሩን ምንጭ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ማህበራዊ መዋቅር ውስጥ፣ አንድ ወላጅ ለልጁ በቤተሰብ ይዞታ ላይ ቤት እንዲሰራ ሲፈቅድ፣ ይህ ድርጊት ወደፊት ሊሻር የሚችል ጊዜያዊ የህግ ፍቃድ ተደርጎ በፍጹም አይታሰብም፡፡ ይህ ቋሚ የሆነ ስጦታና የቤተሰብ ውርስን የፍ/ህ/ቁጥር 1723 ድንጋጌን መሰረት በማድረግ የሚፈፀም ሳይሆን የማህበረሰቡ የባህል አካል ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበረው የተሻረው ውሳኔ ህጋዊ ክፍተት ቢኖረውም ይህንን ማህበራዊ እውነታ ግን ያንጸባርቅ ነበር፡፡ አዲሱ ውሳኔ ግን በፍ/ህ/ቁ 1179 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በቤተሰብ ውስጥ ‘'የተቀበረ ፍንጅ” አድርጎታል፡፡ የቤተሰብ መደጋግፍን፤ መተጋገዝን ወደ አደገኛ የህግ ስምምነት በመለወጥ አንድ የቤተሰብ አባል ከሚመለከተው የመንግስት አካል የተሰጠው የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ስላለው ብቻ ለዘመናት በኖረበት ቤት ላይ የነበረውን ሌላ የቤተሰብ አባል ካሳ እስከከፈለ ድረስ የማስለቀቅ መብት አለው የሚል ዳኝነት በቤተሰብ መካከል ያለውን መተማመንና ባህላዊ ደንቦችን መሰረታዊ በሆነ መንገድ ሽርሽሮ ገደል የሚከት ነው፡፡ የዘመኑን የብዝሃ ህግ ፍልስፍና ባጣጣመ መልኩ ህገ መንግስታዊ እውቅና አግኝቶ በአንዳንድ ክልሎች(ኦሮሚያንና አማራን መጠቀስ ይቻላል) የባህላዊ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ሰጥቶ በመተግበር ላይ ያለውን ባህላዊ ዳኝነትንም አደጋ ውስጥ የሚከት ሁኖ ይገመታል፡፡
እንደሚታወቀው በህግ አተረጓጎም ዓውድ ውስጥ "ማህበራዊ እውነታ" (social reality) የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ፣ ከቀላል የማህበረሰብ ሁኔታ ገለጻ የዘለለ ጥልቅ አንድምታ አለው፡፡ ይህ የህግ አተረጓጎም መርህ የህግ ተርጓሚው አካል ከህግ ውጪ አድርጎ የሚመለከተው ገለልተኛ ጉዳይ ሳይሆን፣ የትርጓሜው ሂደት ወሳኝ አካልና መለኪያ ስለመሆኑ ይታመናል፡፡ የህግን ትርጉምና ተፈጻሚነት ለመወሰን ተገቢው ጥረት በሚደረግበት የዳኝነት ተግባር ውስጥ "ማህበራዊ እውነታ" የተለያየ ሚናን ይጫወታል፡፡ የ''ማህበራዊ እውነታ" መርህ የህጉ ቃል በወረቀት ላይ ከሚሰጠው ትርጉም ውጪ፣ በተግባር መሬት ላይ የሚፈጥረውን እውነተኛ ውጤትና ከህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ህይወት፣ ልማድና እሴት ጋር ያለውን መስተጋብር የሚገልጽ መለኪያ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በዚህ እይታ፣ "ማህበራዊ እውነታ" ማለት የህግ ቃልን በጭፍን መከተል ኢ-ፍትሐዊ ወይም ከህብረተሰቡ ህይወት ጋር የተላቀቀ ውጤት ሲያስከትል የትርጓሜውን አቅጣጫ እንደገና ለማጤን የሚያስገድድ ተግባራዊ ማሳያ (practical evidence) ነው፡፡
ዓላማን መሰረት ካደረገ የህግ አተረጓጎም ዘዴ (Teleological/Purposive Interpretation) አንፃር ሲታይም ይህ መርህ በራሱ "ማህበራዊ እውነታን" እንደ ዋና መነሻ የሚወስድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ህግ የሚወጣው አንድን ማህበራዊ ችግር ለመፍታት፣ ማህበራዊ ግንኙነቶችን ለማስተካከል ወይም የተሻለ ማህበራዊ ሁኔታን ለመፍጠር ነውና፡፡ ስለዚህ በዚህ የትርጓሜ መርህ መሰረት "ማህበራዊ እውነታ" ማለት ህግ አውጪው ሊቀርፈው የፈለገው ማህበራዊ ክስተት (social phenomenon) ወይም ሊያሳካው ያሰበው ማህበራዊ ግብ (social goal) ነው፡፡ በመሆኑ ፍ/ቤቱ ህጉን ሲተረጉም ትርጉሙ ይህንን የመጀመሪያ ማህበራዊ ዓላማ በዘመኑ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ የሚያሳካ መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ይለዋል፡፡ በዚህም ማህበራዊ እውነታ የህግ ትርጓሜ መነሻም መድረሻም ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከስርዓታዊ የህግ አተረጓጎም (Systematic Interpretation) አንጻር ሲታይም ስርዓታዊ የህግ ትርጓሜ ህግን ከሌሎች ህጎች ጋር በአጠቃላይ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ በማየት እንዲተረጎም የሚያዝ በመሆኑ አተረጓጎሙ የህግ ድንጋጌዎችን ብቻ ማካተት ሳይሆን ህጉ የሚሰራበትን አጠቃላይ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አውድም ሊጨምር ይገባል የሚል ፍልስፍና ያለው ነው፡፡ በዚህ እይታ "ማህበራዊ እውነታ" ማለት ህጉ አካል የሆነበት አጠቃላይ ማህበራዊ መዋቅር (broader social structure) ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ አግባብ አንድን የንብረት ህግ ድንጋጌ ስለ ቤተሰብ ከሚደነግጉ ህጎችና ከሀገሪቱ የቤተሰብ እሴቶች ነጥሎ መተርጎም ስህተት ወደሆነ ድምዳሜ ሊያመራ ይችላል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም "ማህበራዊ እውነታ"፣ የህግ ድንጋጌው የሚተነተንበትና ትርጉም የሚሰጥበት ወሳኝ አውድ ሆኖ እንዲያገልግል ሊደረግ ይገባል እንጂ ህግ ተርጓሚው ይህንን እውነታ ችላ ብሎ በቀጥታ ወደ ህጉ በማለፍ የሚሰጠው ዳኝነት ከህብረተሰቡ ህይወት የተነጠለና ትርጉም የለሽ ፤ደረቅ ቃል በመሆኑ ለአደጋ ተጋላጭነቱ ከፍ ያለ በመሆኑ ተመራጭነት ያለው አካሄድ እንዳልሆነ ይታመናል፡፡
ሰፊ አንድምታዎች፡ ኢኮኖሚያዊ ትርጉም ማጣትና አዲስ የዋስትና ዕጦት
ሰበር ችሎቱ በተጠቀሰው መዝገብ የህግ ወግ አጥባቂነትን የአተረጓጎም ስልት አጥብቆ የመጓዙ አቋም የረጅም ጊዜ አንድምታዎች አሳሳቢ ናቸው፡፡ ባለ ሰባት ዳኞች ሰበር ችሎቱ ከማህበራዊ እውነዎች ጋር ተገናዝቦ ተገቢ ግንዛቤ ተይዞ ዳኝነት የተሰጠባቸውን የቀደሙ የተወሰኑትን አስገዳጅ የህግ ትርጉሞችን ሁሉ የላቀና ጠንካራ አሳማኝነት ያለውን ምክንያት ሳያስፍር አስገዳጅ የህግ ትርጉም ስልጣኑን በመጠቀም ብቻ፣ ከማህበራዊ እውነታ ጋር በተፋታ መንገድ ዋጋ አልባ አድርጎ አልፎአል፡፡
አዲሱ ትርጉም በሚሊዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የኑሮ ሁኔታ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ይቸልሳል፡፡ ቀላል ሊባል የማይችል የማህበረሰብ ክፍል ትዳር መስርቶና ልጅ ወልዶ የሚኖረው ከቅርብ ዘመዶቹ ይዞታ ላይ በሰራው ቤት ውስጥ ስለመሆኑ ሳይንሳዊ ጥናት የማያስፈለገው ሀቅ መሆኑ ይታመናል፡፡ አዲሱ አስገዳጅ የሰበር ችሎቱ የህግ ትርጉም በበርካታ ዜጎች ላይ ቀጣይነት ያለውን የማያቋርጥ ስጋትን ይፈጥራል፡፡ የህግ ትርጉሙ ባለይዞታው ካሳ እስከከፈለ ድረስ በማናቸውም ጊዜ ገንቢውን የማስለቀቅ መብት ያለው መሆኑን ያረጋገጠለት በመሆኑ ከህንፃው ገንቢ ጋር የመፍናቀል ስጋት ሁልጊዜ አብሮት እንዲኖር ያደርጋልና፡፡ ይህ የህግ ዋስትና ዕጦት ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን በእጅጉ ያዳክማል፡፡ አንድ ሰው የመኖር ህልውናው ራሱ እርግጠኛ ባልሆነበት ሁኔታ ለምንስ ቢባል ቤቱን ለማስፋፋት በቤቱ ውስጥ ንግድ ለመጀመር ወይም ከፍተኛ የሆነ ማሻሻያ ለማድረግ ይነሳሳል? የሚለው ጥያቄ በራሱ መልስ ሰጭ ነው፡፡ የመፈናቀል ስጋት ሁልጊዜ ባለበት ሁኔታ የኢንቭስትመንት ስራን ለመስራት ሰዋዊ ተፈጥሮ ፈፅሞ አይፈቅድምና፡፡ አዲሱ የሰበር ችሎቱ የህግ አተረጓጎም መንገድ በተለይ በፍጥነት በሚያድጉ ከተሞች ውስጥ ወሳኝ የሆነውን በራስ አቅም የሚደረግ የመኖሪያ ቤት ልማትን በእጅጉ የማቀጨጭ ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡
በሰበር ችሎቱ ትንታኔ ግልፅ ስለመሆኑ በታመነው ድንጋጌ የተቀመጠው የህግ መፍትሄ የሆነው "ካሳ" ራሱ ማህበራዊ እውነታን ለመተካት ብቁ አይደለም፡፡ አንድ ቤት የገበያ ዋጋ ያለው ህንጻ ብቻ አይደለም፡፡ የማህበራዊ ካፒታል፣ የማህበረሰብ ትስስር፣ የልጆች ትምህርት ቤት፣ የስራ ቦታ እና የግል ማንነት ማዕከል ነው፡፡ መፈናቀል በካሳም ቢሆን ሰዎችንና ቤተሰቦችን ከተመሰረተ ህይወታቸው የሚነቅል ማህበራዊ ጥቃት መሆኑ ይታመናል፡፡ አሁን ካለው የካሳ አገማመት ስርዓት አንፃር ሲታይ በማናቸውም መለኪያ ካሳ ሊባል የሚችል አይደለም፤ ባለይዞታውን ያላግባብ የማበልፀግ እድሉ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡
በመጨረሻም ይህ ውሳኔ የሀገሪቱ የዳኝነት አካል ቁንጮ የሆነው እና የዳኝነት አስተምህሮን ያዳብራል ተብሎ የሚታመነው ሰበር ሰሚ ችሎት በሰባት ዳኞች ችሎት የህግ ወግ አጥባቂነት ፍልስፍን ከሌሎች መሰረታዊ የህግ አተረጓጎም መርሆዎች በማስቀደም የያዘውን ድምዳሜ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ከላይ በተደጋጋሚ እንደተገለፀ ችሎቱ የህግን ቃል ከማህበራዊ አንድምታውና ከፍትሐዊነት መርሆዎች ነጥሎ መተርጎም የዳኝነት ዋነኛ ተግባር ነው የሚል እምነት ያለውን የህግ ወግ አጥባቂነት አስተምህሮ ተቀብሏል፡፡ ህግ ሊተረጎም የሚገባው ከሚያስከትለው እውነተኛ ውጤትና ከሚሰራበት ማህበራዊ አውድ አንጻር ነው የሚለውን የህግ እውነታነት አስተሳሰብ ግን በግልፅ ሳይመረምር በዝምታ ቀብሮት ውድቅ አድርጓል፡፡ ችሎቱ በህግ የተጠበቁ መብቶችን ከፍትሐዊነት መርሆዎች ጋር የሚያመጣጥን፣ ይበልጥ ጥልቅ የሆነ የአተረጓጎም ደንብ የመቅረጽ ዕድል ነበረው፡፡ ለምሳሌ፣ "በመብት ላይ መዘግየት" ወይም "ፍትሐዊ ማገድ" (Principle of Estoppel) ወይም ርትዕ /Equity/ የሚሉ አስተምህሮዎችን ለአገሪቱ የዳኝነት ስርዓት በማስተዋወቅ፣ ሆን ብሎ "በመብቱ ላይ የተኛ" የይዞታ ባለመብት ከረጅም ጊዜ በኋላ መብቱን በመጠቀም በቅን ልቦና ህይወቱን በመሰረተ ገንቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያደርስ መከላከል ይችል ነበር፡፡ እንዲህ አይነቱን የፍትሐዊነት ከለላ ከመፍጠር በመቆጠብ ችሎቱ ወረቀት ላይ ያለውን ቃል ብቻ በማየት ወጥ የሆነ ደንብን መርጧል፡፡ ይህም እርግጠኝነትንና ተገማችነትን ሊያስገኝ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ወደፊት በሚታዩ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ጉዳዮች ላይ ፍትሐዊነትን መስዋዕት ማድረጉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በሁዋላ የወጣውን ህገ መንግስትን ቀድሞ ከወጣው ዝቅተኛ ህግ ጋር በማጣጣም መተርጎም ስለሚቻልበት አግባብ አብራራ!
የማጣጣም ትርጉም ስልት ያላግባብ ስራ ላይ ስለመዋሉ
ሰበር ችሎቱ በጉዳዩ ላይ የትርጉም ለውጥ ሲደርግ ከተጠቀማቸው የህግ አተረጓጎም ስልቶች አንዱ"የማጣጣም የትርጓሜ መርህን" (Principle of Harmonious Interpretation) ሲሆን የፍርዱ ሀተታ ይዘት ሲታይም በ1960 በወጣው የፍታብሔር ሕግ አንቀጽ 1178 እና 1179 የተቀመጡት ድንጋጌዎች እና በ1995 በጸደቀው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ድንጋጌ መካከል ያለውን ግንኙነት መመርመር ተገቢ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሆኖም ሁለቱን ሕጎች "የማጣጣም የትርጓሜ መርህን" (Principle of Harmonious Interpretation) በመጠቀም ማስታረቅ ይቻል እንደሆነ መመርመር ግን ወሳኝ ነበር። በዚህም ምሰረት በሁለቱ ሕጎች መካከል ያለው ልዩነት በቀላሉ በትርጓሜ ሊስተካከል የሚችል የአሻሚነት ጉዳይ ሳይሆን፣ ከመሠረታዊ የሕግ ፍልስፍና የሚመነጭና ፈጽሞ ሊታረቅ የማይችል ቀጥተኛ ቅራኔ ይታያል የሚል እምነት አለኝ። በመሆኑም የማጣጣም የትርጓሜ መርህ በዚህ ጉዳይ ላይ ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም። የዚህ ቅራኔ መሠረታዊ ምንጭ የሚቀዳው፣ ሁለቱ ሕጎች ስለ መሬት ባለቤትነት ካላቸው ፍጹም ተቃራኒ መነሻ ነው። የፍትሓ ብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች የተመሠረቱት መሬት በግለሰቦች የግል ባለቤትነት ሥር ሊሆን ይችላል በሚል የሊበራል የንብረት መብት ፍልስፍና ላይ ነው። "ባለመሬት" (landowner) የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ በራሱ፣ አንድ ግለሰብ መሬቱን የመሸጥ፣ የመለወጥና እንደፈለገ የመጠቀም ፍጹም መብት እንዳለው ያመለክታል። የአንቀጽ 1178 እና 1179 አጠቃላይ አመክንዮ የተገነባው በዚህ የግል ባለቤትነት መብት ላይ ሲሆን፣ በመሬቱ ባለቤትና በላዩ ላይ ሕንፃ በሠራ ሌላ ወገን መካከል የሚፈጠረውን የንብረት ክርክር ለመፍታት ባለመ እይታ ነው። በተቃራኒው የ1995 ሕገ መንግሥት ይህንን የሕግ ፍልስፍና ሥር-ነቀል በሆነ መልኩ ለውጦታል። የህገ መንግስቱ አንቀጽ 40(3) የመሬት ባለቤትነት የመንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብቻ መሆኑን በማያሻማ ቋንቋ ይደነግጋል፡፡ እንዲሁም መሬት ከገበያ ዑደት ውጭ መሆኑን በማረጋገጥ ሊሸጥና ሊለወጥ እንደማይችል በይፋ ያውጃል። ይህ ድንጋጌ የፍትሓ ብሔር ሕጉ የተመሠረተበትን "የግል የመሬት ባለቤትነት" ጽንሰ-ሐሳብ ከነአካቴው በመሻር የሕግ መሠረቱን ያሳጣ መሆኑ ይታመናል። በመሆኑም፣ የማጣጣም የትርጓሜ መርህ ዋና ዓላማ የሆነውን አሻሚ የሆኑ ድንጋጌዎችን ከበላይ ሕግ ጋር ለማስማማት መሞከር እዚህ ላይ ትርጉም ያጣል። ምክንያቱም ችግሩ የቃላት አሻሚነት ሳይሆን፣ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ሁለት የተለያዩ የሕግ ሥርዓቶች መኖር ነው። የሌለውን "የግል ባለመሬት" መብት ለማስከበር የወጣን ሕግ፣ ያንን መብት ከሕግ ውጭ ካደረገ ሕገ መንግሥት ጋር ማጣጣም በምንም መልኩ አይቻልም። ከዚህም ባሻገር፣ ሕገ መንግሥቱ የድሮውን ሥርዓት ከመሻሩም በላይ፣ ለጉዳዩ አዲስና ራሱን የቻለ መፍትሔ አስቀምጧል። አንቀጽ 40(7) በመሬት ላይ ያለውን የመጠቀም መብትና በላዩ ላይ በሚገነባ የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለውን የባለቤትነት መብት በግልጽ ይለያል። በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ሰው በጉልበቱ ወይም በካፒታሉ የገነባው ሕንፃ ወይም ያደረገው ማሻሻያ የራሱ የግል ንብረት ሲሆን ይህ መብቱ በመሬቱ ላይ ካለው የመጠቀም መብት የተለየ ነው። ይህ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ በፍብትሓ ሔር ሕጉ አንቀጽ 1178 እና 1179 ለመፍታት የታሰበውን ችግር በአዲስ መልክ ስለሚፈታው፣ የቆዩትን ድንጋጌዎች ከነአካቴው አላስፈላጊና ተፈጻሚነት የሌላቸው ያደርጋቸዋል፡፡ ስለሆነም በፍትሓ ብሔር ሕጉና በሕገ መንግሥቱ መካከል ያለው ግጭት የቃላት አጠቃቀም ሳይሆን የመሠረታዊ የሕግ መርህ ልዩነት በመሆኑ፣ ሊጣጣም የማይችል ቅራኔ ፈጥሯል። የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች የፍታብሔር ሕጉን መሠረታዊ መነሻ ሙሉ በሙሉ የሻሩ በመሆናቸው፣ ፍርድ ቤቶች እነዚህን የፍታብሔር ሕግ አንቀጾች ወደ ጎን በመተው የሕገ መንግሥቱን የበላይነትና ቀጥተኛ ድንጋጌዎች የማስከበር ግዴታ አለባቸው። ከዚሀ አንፃር ሲታይ ችሎቱ በጉዳዩ ላይ "የማጣጣም የትርጓሜ መርህን" (Principle of Harmonious Interpretation) ተግባራዊ ያደረገበት አግባብም የህግ አተረጓጎም ደንቦችን እንዲሁም የማህበረሰባዊ ህግ እይታዎችን ያላገናዘበ ሁኖ ይገኛል፡፡
ማጠቃለያ
ባለሰባት ዳኞች ሰበር ሰሚ ችሎት ወረቀት ላይ ያለውን ህግ ላይ ላዩን በማየት እና በርካታ የህግ ማዕቀፎችን በመጠቃቀስ የተዋጣለትና በአስተምህሮ ደረጃ አስፈላጊ የሆነ ውሳኔ ሰጥቶአል ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ለሚጋጩ የሰበር ትርጉሞች ወጥነት ማስፈኑ ግን አይከፋም፡፡ የንብረት ህግ አስተምህሮን ከህገ-መንግስታዊ መርሆዎች ጋር ለማጣጣም ጥረት ያደረገ ቢሆንም የህገ መንግስት ትርጉሙን የወሰደበት አግባብ ግን ከአስገዳጅ የህገ መንግስት ትርጉም ስርዓት ጋር በጥንቃቄ አይቶአል ለማለት የማያስችል ነው፡፡ ውሳኔው ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ዋጋን የማስከፍል ሃይል ያለው ነው፡፡ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የንብረት ግንኙነቶችን የሚገዙትን ጥልቅ ባህላዊና ቤተሰባዊ ደንቦችን ከማስተናገድ በመቆጠብ፣ ችሎቱ ይፋዊ መሰረት ያለው ነገር ግን በማህበራዊ ደረጃ ስብራት ያለበትን ዳኝነት አስተላልፏል፡፡ ውሳኔው ክርክሮችን እንደሚያባብስ፣ ለረጅም ጊዜ የቆዩ የኑሮ ስምምነቶችን እንደሚያናጋ እና አዲስ የህግ ተጋላጭ ዜጎችን እንደሚፈጥር አጣራጣሪነት አለው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ይህ ውሳኔ በወረቀት ላይ ባለው ህግና በተግባር ላይ ባለው ህግ መካከል ያለውን ውጥረት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሲሆን የህግ ወግ አጥባቂነት የትርጉም ዘዴ/ ፎርማሊዝም/ ከማህበራዊ እውነታ ጋር ሳይቃኝ ሲቀር ሊጠፋ ስለሚችለው እሴት እንደ የማስጠንቀቂያ ደወል ሁኖ የሚያግለግልም ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም የውሳኔው ተፈፃሚነት በህገ መንግስት ተርጓሚ አካል ታይቶ ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተጨባጭ እውነታ ጋር የተጣጣመ ህገ መንግስታዊ ትርጉም ሊሰጥበት የሚችል እድል መኖሩ የሚታመን ቢሆንም ለጊዜው ግን አደጋው ከፍ ያለ ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትል ነው፡፡
The content of this article is intended to provide a general guide to the subject matter. Specialist advice should be sought about your specific circumstances.
[View Source]